ማንቸስተር ዩናይትድ በድጋሚ ወደ መጀመሪያው ምዕራፍ ተመለሰ
ሌላ አሰልጣኝ ተሰናብቷል፣ ሌላ ከባድ ውሳኔም ይጠበቃል
የሩበን አሞሪም መባረርን ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድ በድጋሚ አዲስ አሰልጣኝ ፍለጋ ላይ ይገኛል። እ.ኤ.አ. በ2013 ስር አሌክስ ፈርጉሰን ጡረታ ከወጡ በኋላ ክለቡ ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ ለመጀመር ሲገደድ ይህ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
በእያንዳንዱ ጊዜ ከኦልድ ትራፎርድ የሚወጣው መልዕክት ተመሳሳይ ነው ይህ ሹመት ትክክለኛው መሆን አለበት። ነገር ግን በእያንዳንዱ ጊዜ ዩናይትድ በአለም እግር ኳስ ውስጥ ትልቁን ችግር መፍታት ተስኖታል ይህም ኃላፊነቱን በትክክል መሸከም የሚችል ሰው ማግኘት ነው።
ይህ ቀላል የስራ ድርሻ አይደለም። ማንቸስተር ዩናይትድን ማሰልጠን በስፖርቱ ዓለም ውስጥ ካሉ እጅግ ከባድ ስራዎች አንዱ ነው።

ይህ የስራ ድርሻ አሰልጣኞችን ለምን ያዳክማል?
ዩናይትድ ዝም በሎ የእግር ኳስ ክለብ አይደለም። ከፍተኛ ድምፅ ያለው፣ በፖለቲካ የተተበተበ እና ዘወትር የሚገመገም ክለብ ነው። የቀድሞ ተጫዋቾች መገናኛ ብዙሀኑን ይቆጣጠራሉ፣ ደጋፊዎች የማጥቃት እግር ኳስን ይጠብቃሉ፣ ጫናውም ወዲያውኑ ይመጣል።
ከፈርጉሰን በኋላ እያንዳንዱ ተመራጭ በተለያየ መንገድ ሳይሳካለት ቀርቷል። ዴቪድ ሞይስ በጫናው ተሸነፈ። ሉዊ ቫን ሃል በጣም ግትር ነበሩ። ሆሴ ሞሪንሆ ልምዱ ቢኖራቸውም የመጡት ግን በጣም ዘግይተው ነበር። ኦሌ ጉናር ሶልሻየር ተሰሚነት አጡ። ኤሪክ ቴን ሀግ እና አሞሪም ሁለቱም ከኃላፊነታቸው ጋር ታግለዋል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሞሪም በስፖርቲንግ ሊዝበን ስኬታማ ቢሆንም፣ ለዚህ ስራ ዝግጁ አልነበረም። ለሁኔታዎች ተለዋዋጭ እንደሚሆን ቃል ቢገባም በራሱ የጨዋታ ስልት ላይ ብቻ ሙጥኝ ብሏል። የሚሰነዘሩ ትችቶችን እና በየቀኑ በክለቡ ዙሪያ የሚሰማውን ወሬ ለመቋቋም ተቸግሯል። በመጨረሻም ዩናይትድ በድጋሚ ዋጋ ከፍሏል።
ዩናይትድ በዕድል መጫወቱን ማቆም አለበት
በዚህ ጊዜ ዩናይትድ ሌላ ስጋት ውስጥ መግባት አይችልም። ክለቡ የፕሮጀክት አሰልጣኝ ወይም ብቅ እያለ ያለ ተሰጥኦ የሚመጣ አሰልጣኝ አያስፈልገውም። ይልቁንም ተሰሚነት፣ ልምድ እና ብቃት ያለው ውጤታማ ልሂቅ አሰልጣኝ ያስፈልገዋል።
እንደ ቶማስ ቱሄል፣ ካርሎ አንቸሎቲ እና ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ያሉ ስሞች ይህንን መገለጫ ያሟላሉ። መጠበቅ ህመም ሊኖረው ቢችልም፣ ሌላ የዕድል ሙከራ ግን አስከፊ ሊሆን ይችላል። ወንበሩን ለመሙላት ብቻ ተብሎ አንድን ሰው በፍጥነት መሾም እስካሁን ብዙ ጊዜ ሳይሳካ ቀርቷል።
ክለቡ ምን እንደሚፈልግ መወሰን አለበት እውነተኛ መሪ ወይስ ሌላ ጊዜያዊ መፍትሄ?
ከታክቲክ በላይ ስብዕና የተሻለ ዋጋ አለው
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘወትር እንደሚናገሩት አሰልጣኙ በክለቡ ውስጥ ትልቁ ስብዕና ሊኖረው ይገባል። በአሁኑ ሰዓት ግን ዩናይትድ በአሰልጣኞች መቀመጫ አካባቢ እንዲህ ያለ ሰው የለውም።
ይህ ጠንካራ መሪ የሚፈልግ ትልቅ ክለብ ቢሆንም፣ ጠንካራ መሪ ግን የለውም። ይህ እስካልተቀየረ ድረስ ታክቲክም ሆነ የዝውውር ጉዳዮች ትርጉም አይኖራቸውም፤ እድገቱም ዝግተኛ ሆኖ ይቀጥላል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የሚያስፈልገው ጫናውን ተቋቁሞ፣ ትርክቱን ተቆጣጥሮ ማሸነፍ የሚችል ሰው እንጂ ለመቆየት ብቻ የሚታገል አይደለም።
ይህን ታሪኩን ለመቀየር የመጨረሻው ጊዜ ነው።


