የአንድ አፍታ አስገራሚ ጥበብ ደቡብ አፍሪካን ታደጋት፤ አንጎላ ግን ጥረቷ ሳይሳካ ቀርቷል
ደቡብ አፍሪካ በመጨረሻም በመክፈቻ ጨዋታ ድል ቀንቷታል
ደቡብ አፍሪካ በማራኬሽ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ‘ለ’ መክፈቻ ጨዋታ አንጎላን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ፣ ለ21 ዓመታት በአህጉራዊው መድረክ የመክፈቻ ጨዋታን ለማሸነፍ ስታደርግ የነበረውን ጥበቃ አብቅታለች።
ድሉ በቀላሉ የመጣ አልነበረም። ባፋና ባፋናዎች በርካታ የግብ እድሎችን በመፍጠር አደገኛ የነበረችውን አንጎላን ለማሸነፍ፤ ጥንካሬ፣ ትዕግስት እና የአንድ ተጫዋች ልዩ ብቃት አስፈልጓቸዋል። አንጎላ በበኩሏ ከጨዋታው ቢያንስ ነጥብ ይዛ ለመውጣት የሚያስችሏትን በቂ እድሎች መፍጠር ችላ ነበር።
ከጅምሩ መቆጣጠር ግብ አስገኝትዋል
ደቡብ አፍሪካ ጨዋታውን በራስ መተማመን የጀመረች ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም ኳስን ተቆጣጥራ በመጫወት ጥሩ ቆይታ አድርጋለች። ይህ ግፊቷም በ21ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል፤ ኦስዊን አፖሊስ በሳጥን ውስጥ አስደናቂ የሆነ የኳስ ቁጥጥር በማሳየት ሁለት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ፣ መሬት ለመሬት በረገጠች ኳስ በግቡ የታችኛው ጥግ በኩል አስቆጥሯል።
ግቡ የደቡብ አፍሪካን ጠንካራ አጀማመር በግልጽ ያሳየ ሲሆን፤ አንጎላውያን በበኩላቸው የጨዋታውን ፍጥነት መቋቋም ተስኗቸው ወደ መከላከል እንዲያፈገፍጉ ተገደው ነበር።
አንጎላ ከእረፍት በፊት ምላሽ ሰጥታለች
አንጎላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻለች ሲሆን፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረውም አቻ ሆናለች። ፍሬዲ ዝቅ አድርጎ የመታው የቅጣት ምት በደቡብ አፍሪካ የግብ ክልል ውስጥ መደናገርን የፈጠረ ሲሆን፣ “ሾው” ከሁሉ ቀድሞ ኳሷን በማግኘት ወደ ግብነት በመቀየር ወሳኝ ንክኪ አድርጓል።
የአቻነቷ ግብ የጨዋታውን ግለት የለወጠች ሲሆን፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጠናቀቅም ሁለቱም ቡድኖች እኩል ፉክክር እያደረጉ እንዲወጡ አስችሏል።
አስገራሚ ክስተቶች፣ የቪኤአር (VAR) ውሳኔ እና የግቡ አግዳሚ
ደቡብ አፍሪካ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ተቀይሮ የገባው ሼፓንግ ሞሬሚ ኳሷን በረጋ መንፈስ መረቡ ላይ ሲያሳርፍ ዳግም መሪ የሆኑ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን ቪኤአር (VAR) ጣልቃ በመግባት ላይል ፎስተር በተሳተፈበት የጥቃት አጀማመር ላይ ከጨዋታ ውጪ (offside) በመኖሩ ግቧን ሳያጸድቃት ቀርቷል።
ከጥቂት ቅጽበቶች በኋላም እምበከዘሊ እምቦካዚ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በመመለሱ፣ ደቡብ አፍሪካ መሪ ለመሆን በጣም ተቃርባ ነበር፤ አንጎላውያንም በዚህ አጋጣሚ በእድል ተርፈዋል።
ፎስተር ወሳኙን ግብ አስቆጥሯል
በመጨረሻም በ79ኛው ደቂቃ የናፈቀው ግብ ተገኝቷል። ፎስተር ከግብ ክልል 20 ያርድ ገደማ ርቀት ላይ ኳሷን ተቆጣጥሮ፣ በሚገርም ሁኔታ አሽከርክሮ በመምታት በግቡ የላይኛው ጥግ ላይ አሳርፏታል። ይህም የጨዋታው ታሪካዊና ወሳኝ አፍታ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህ ጎል የደቡብ አፍሪካን ውጤታማነት እና የረጋ መንፈስ በግልጽ ያሳየ ሲሆን፤ እነዚህም ባህሪያት ቡድኑ ውጥረት የነገሰበትን የመጨረሻ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በብቃት ተሻግሮ ሙሉ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ረድተውታል።ቤልጂየማዊው አሰልጣኝ ሁጎ ብሩስ ከቡድናቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ይልቅ በውጤቱ መደሰታቸው አይቀሬ ነው፤ ይህ ድል ደቡብ አፍሪካን ወደ ኖክ አውት ለማለፍ በምታደርገው ጉዞ ላይ ጠንካራ መሠረት ጥሏታል። የምድብ ‘ለ’ ጨዋታዎች ሲቀጥሉ፣ ዛሬ ሰኞ አመሻሹን ግብፅ ከዚምባብዌ ጋር ይጋጠማሉ።

