አለም አቀፍየሁሉም ኳስ ግጥሚያዎች

አማድ ዲያሎ አይቮሪኮስትን እየመራ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ አሸጋግሯል

ሻምፒዮናዎቹ በማራኬሽ ምን ያህል ብቁ እንደሆኑ በተግባር አሳይተዋል

የአፍሪካ ዋንጫ ተከላካይ ሻምፒዮኗ አይቮሪኮስት ጎረቤቷን ቡርኪና ፋሶን ማራኬሽ ላይ 3 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ለሩብ ፍፃሜው መድረሷን አረጋግጣለች። በዚህ ጨዋታም አማድ ዲያሎ በድጋሚ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተረጋጋና ውጤት የሚወስን ብቃቱን በማሳየት የጨዋታው ኮከብ ሆኖ አምሽቷል።.

እ.ኤ.አ. በ2024 በራሳቸው ሜዳና በደጋፊያቸው ፊት የሻምፒዮናነትን ክብር የተቀዳጁት “ዝሆኖቹ” ፤ በመጪው ቅዳሜ አጋዲር ላይ ከግብፅ እና መሐመድ ሳላህ ጋር ለሚደረገው ታላቅ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ ተዘጋጅተዋል። በዚህም ድላቸው፤ ከ2010 ወዲህ ዋንጫውን ይዘው ውድድሩን የጀመሩና በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድል በመቀዳጀት ሻምፒዮናነታቸውን ለማስከበር የተሳካላቸው የመጀመሪያው ቡድን ለመሆን በቅተዋል።

አማድ ዲያሎ አይቮሪኮስትን እየመራ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ አሸጋግሯል
https://www.nytimes.com/athletic/live-blogs/ivory-coast-vs-burkina-faso-live-updates-afcon-2025-score-result/FfTgSw4FsRGH/

አማድ በመጀመሪያው አጋማሽ ለታየው የበላይነት መነሳሳትን ፈጥሯል

አይቮሪኮስት ጨዋታውን ገና በጠዋቱ የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ የአማድ ፍጥነትና የማታለል ብቃት ለቡርኪና ፋሶ ተከላካዮች ፈተና ሆኖባቸዋል። የማንቸስተር ዩናይትዱን የክንፍ መስመር ተጫዋች ጎትቶ የጣለው አዳሞ ናጋሎ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ቢጫ ካርድ የተመለከተ ሲሆን፣ ጥቂት ቆይቶም አማድ ግብ ጠባቂው ሄርቬ ኮፊን ለከባድ መከላከል ዳርጎታል።

ጫናው እየበረታ ሲሄድ ካፒቴኑ ፍራንክ ኬሴ ሁለት ጊዜ ለግብ ተቃርቦ ነበር፤ ሆኖም የመክፈቻዋ ግብ የተገኘችው በ20ኛው ደቂቃ ላይ ነው። ኢቫን ጊሳንድ ኳስ ለመንጠቅ ካደረገው ትግል በኋላ፣ አማድ በሳጥኑ ውስጥ ሶስት ተከላካዮችን በድንቅ ክህሎት አልፎ ኳሷን በኮፊ ላይ በማሳረፍ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል።

ቡርኪና ፋሶዎች ግቡ ከመቆጠሩ በፊት ጥፋት  ተሰርቷል በሚል ተቃውሞ ቢያሰሙም፣ በቪኤአር  ምርመራ ግን ግቡ መጽደቁ ተረጋግጧል። “ፈረሰኞቹ”  ራሳቸውን ለማረጋጋት እንኳን ፋታ ሳያገኙ አይቮሪኮስት በድጋሚ መረባቸውን ደፍረዋል። አማድ በቀኝ መስመር በኩል ሰንጥቆ በመግባት አመቺ ኳስ ለታዳጊው ተሰጥኦ ያን ዲዮማንዴ ያቀበለው ሲሆን፣ እርሱም በ32ኛው ደቂቃ ላይ ኳሷን በኃይል መረብ ላይ በማሳረፍ ውጤቱን 2 ለ 0 አድርጎታል።

ቡርኪና ፋሶዎች ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም አይቮሪኮስት ግን እንደጸኑ ቀጥለዋል

“ፈረሰኞቹ” ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደረጉ ሲሆን፣ ዳንጎ ዋታራ ከእረፍት በፊት ኳስና ዘንግ አጋጭቶ ለጥቂት ጊዜ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ከእረፍት መልስ ቡርኪና ፋሶዎች የጨዋታውን ፍጥነት የጨመሩ ሲሆን፣ ዋታራም ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ በድጋሚ ያያ ፎፋናን ፈትኖታል።

ምንም እንኳን ጫና ቢደረግባቸውም፣ አይቮሪኮስቶች ረጋ ብለው መጫወታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በተቃራኒ ጥቃትም ሁሌም ቢሆን አደገኛ መስለው ታይተዋል።

ቱሬ ድሉን ሲያረጋግጥ ትኩረት አሁን ወደ ግብፅ ጨዋታ ዙሯል

በ87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ባዙማና ቱሬ ሶስተኛውን ግብ በማስቆጠር ያንዣበበውን ማንኛውንም ጥርጣሬ አስወግዷል። ይህ የ19 ዓመት ወጣት ከሜዳው ክፍል በጥሶ በመውጣት በግብ ጠባቂው አቅራቢያ በኩል በልበ ሙሉነት ግቧን ከመረብ ያገናኘ ሲሆን፣ ይህም በውድድሩ ላይ በድንቅ ብቃት ብቅ ካሉ ተጫዋቾች አንዱ መሆኑን ያረጋገጠበት ነበር።

አይቮሪኮስት አሁን ትኩረቷን በሩብ ፍፃሜ ታሪኳ ወደምትታወቀው ግብፅ አዙራለች። አማድ ዲያሎ ባለበት እጅግ ምርጥ ብቃትና ቡድኑ እያሳየ ባለው መነሳሳት፣ የሻምፒዮናዎቹ ዋንጫን የማስከበር ጉዞ አሁንም በጠንካራ ሁኔታ ቀጥሏል።

Related Articles

Back to top button