አንበሶቹ ዘግይተው ቢሆን አግስተዋል፤ ሴኔጋል ምድቧን በበላይነት አጠናቀቀች
ሴኔጋል ለተፎካካሪዎቿ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች
ሴኔጋል በ2025 የቶታል ኢነርጂስ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ቤኒንን በተረጋጋ እና ቁርጠኝነት በተሞላ ብቃት 3-0 በማሸነፍ በምድብ ዲ አንደኛነቷን አረጋግጣለች። በዚህም ለሌሎች ተፎካካሪዎቿ ግልጽ ማስጠንቀቂያ አስተላልፋለች።
ቁጥጥር፣ ትዕግስት እና አስደሳች ክስተቶች በታዩበት በዚህ ጨዋታ፣ የቀድሞዎቹ ሻምፒዮኖች በአስር ተጫዋች ቢቀነሱም ያላቸውን ጥልቀት እና ብስለት በማሳየት ለዋንጫው እውነተኛ ተፎካካሪ መሆናቸውን በድጋሚ አስመስክረዋል።
የቆሙ ኳሶች ለሴኔጋል ብልጫን ሰጥተዋል
ሴኔጋል ጨዋታውን በጥሩ ፍላጎት የጀመረች ሲሆን፣ ኳስን በፍጥነት በማንሸራሸር ቤኒንን በገዛ ክልሏ ለረጅም ደቂቃዎች አጥብቃ ይዛለች። የጥረትዋም ውጤት በ38ኛው ደቂቃ ላይ ታይቷል፤ አብዱላዬ ሴክ ከክሬፒን ዲያታ የተሻማውን ድንቅ የቆመ ኳስ በግንባር በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ይህም ሴኔጋል በመጀመሪያው አጋማሽ ላሳየችው የበላይነት የሚገባ ውጤት ሲሆን፣ ቤኒኖች በመሃል ሜዳ ላይ ለመቆጣጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ማኔ አመቻችቶ አቀበለ፤ ሴኔጋል መሪነቷን አጠናከረች
ከእረፍት መልስ ቤኒኖች በከፍተኛ መነሳሳት በአይዬጉን ቶሲን እና በጁኒየር ኦላይታን አማካኝነት ኤዱዋርድ ሜንዲን ለመፈተን ቢሞክሩም፣ የሴኔጋል በመከላከል ግን ሳይበገሩ ቆይቷዋል። ወሳኙ ሁለተኛ ጎል የተቆጠረው ጨዋታው አንድ ሰዓት ካለፈው በኋላ ነበር። በጨዋታው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የነበረው ሳዲዮ ማኔ፣ በብልሀት ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ሀቢብ ዲያሎ በተረጋጋ አጨራረስ ወደ ጎል ቀይሮት የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።
የቀይ ካርድ ድራማው ሴኔጋልን አላደናቀፋትም
በ71ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው ድንገተኛ መልክ ቀይሯል፤ ካፒቴን ካሊዱ ኩሊባሊ በቪኤአር ምክንያት ቀይ ካርድ ተመዞበት ከሜዳ በመውጣቱ ሴኔጋል ቀሪውን ደቂቃ በአስር ተጫዋች እንድትከላከል ተገዳ ነበር። ቤኒኖች የጎል ዕድል ለመፈለግ ወደ ፊት ቢገፉም እና ግብ ጠባቂው ሜንዲ በተከታታይ ኳሶችን እንዲያድን ቢያስገድዱትም፣ ሴኔጋሎች ጫናውን በተረረጋ መንፈስ በመቋቋም ትክክለኛውን ሰዓት ሲጠባበቁ ቆይተዋል።
ያ ሰዓትም በጭማሪ ደቂቃ ላይ ተከሰተ። ኢብራሂም ምባዬ በሳጥን ውስጥ ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ቼሪፍ ንዲያዬ በተረረጋ ሁኔታ ወደ ጎል ቀይሮት ውጤቱን 3-0 አድርጓል።
የምድቡ አሸናፊዎች በከፍተኛ መነሳሳት ላይ ናቸው
ይህ ድል ሴኔጋልን የምድብ ዲ አሸናፊ ሲያደርጋት፣ ቤኒንም ካሏት ውጤቶች አንጻር ከምርጥ ሶስተኛ ቡድኖች አንዷ በመሆን ወደ 16ቱ ውስጥ መግባት ችላለች። በከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር፣ በጥልቀት እና በፅናት የታጀበችው ሴኔጋል፣ አሁን ሙሉ በራስ መተማመን ሰንቃ ወደ ቀጣዩ ማጣሪያ ተሸጋግራለች።


